Tuesday, January 12, 2016



አብሮ መሮጥ
ኒያላ እንኳን ባቅሟ ከሰው ልጅ ጀግና
ትንባሆን ሽሽት ነው የምትሮጠውና
እንስሳ እንኳን ባቅሙ በሮጠበት ዘመን
አብረህ እሩጥ እንጂ ለብቻ አትታጠን::

ናሆም ታደሰ


Wednesday, August 26, 2015



ማዶ ለማዶ

እዚህ ማዶ አንድ ጎመን እዚያ ማዶ አንድ ጎመን
የእኛማ ጋሽዬ ሊሄዱ ነው ጀርመን::
እዚህ ማዶ… እዞያ ማዶ…
እዚና እዛ ማዶ በርቀት ዘምሮ
ቁራሽ  ስንዴ ጉርሻ ጣሳ ጠላ ማትሮ
በዝማሬው ሳይቀር በግጥሞቹ ቃላት አጥናፍ የሰነገን
በምን ያቀርቡታል ተራርቆ ያደገን?
የለመዳት እፍኝ ከእማምዬ ጓዳ ተጋግራ እንድትቆየው
ቅርበት አይዘምርም ርቀት ነው ሚታየው::
ፊት የሚጠብቀው ቁራሽ ፍርፋሪ
ከጎኑ ዞር ቢል ሆ ሚል አጫፋሪ
ታድያ አጅሬ ይሄኔ
እዚህ ማዶ ብሎ እዚው አይጨርስም እዛ ማዶ ይሄዳል
አድጎ ገንጥሉኝ ቢል በማን ይፈረዳል?

ናሆም ታደሰ
የልጅነት ተፅእኖ በጉልምስና አሻራ አለው

ምስለ ማሲንቆ

አወይ ማሲንቆዬ…
በፈረሱ ጭራ ለስልሳ የተቃኘች
ከላይ ስነካካት ከስር ገዝግዝ አለች።
እኔ መቼ ገባኝ
ለካ የሲቃው ባቲ ጣፋጭ የሚሆነው
ከስርም እንደላይ ሲገዘግዙት ነው።
ካንቺ ባቆራኘኝ የሙዚቃ ዘመን
እኔ እያለው በይወት ከሌላ ገዝጋዥ እጅ ወድቀሽ ያየሁሽ ቀን
በመገዝገዣዬ ደካማነት ባምንም
ሙዚቀኛሽ እኔ ራስ ወዳድ አልሆንም።
በስልቱ የተካነ በዜማው ከጠራሽ
የሌላ አዝማሪ ግዝገዛ ከረታሽ
እኔ ራሴ ወስጄ ልስጥሽ ለዛ አዝማሪ
በጣቶቹ ርኪ በግዝገዛው ኑሪ
ሂጂ ማሲንቆዬ ለፈረስሽ ጭራ
የሚመጥን ገዝጋዥ ወዳለበት ስፍራ።
ምክንያቱም ትዝታሽ ጣፋጭ የሚሆነው
አምባሰል አንቺሆዬሽ ግሩም የሚሆነው
ከስርም እንደላይ ሲገዘግዙሽ ነው።


ናሆም ታደሰ
100# 50 እና 10 ብር
የቸገረኝ ቀን ነው የተራብኩኝ ሰዓት
100# 50 እና 10 ብር የሰጡኝ አባት
ይህ መቶ ብር ማለት አባወራው ገንዘብ
ዝግጁ ነውና ሲርብህ ለማጥገብ
ለኦና ጎተራህ ለራበው ስልቻህ መፍትሄ ስላለው
የብር አረንጓዴን ልምላሜ በለው::
ደሞ እንካ 50 ብርን ቀለሟ ቢጫ ነች
መቶ ጋ ለመድረስ ተስፋ ትሆንሀለች::
ስለዚህ ቢጫዋን ተስፋ ብለህ ጥራት
ካባወራው ስፍራ የሚጥል መሰላል ስለምታይባት::
50ን በዚህ እናብቃ
መቼም ሠው አይኖርም በተስፋ ዘላለም
ከስር የምታያት ይቺ ቀይ ቀለም
አንድ የጎዳና ልጅ ርሀብ የፀናበት
እንደሰማይ ኮከብ ተስፋው የራቀበት
ሺ ግዜ ቢናጥጥ ኪሱ ምታገኘው
ስንት መስዋት ሆኖ የመነተፋትን ይቺን 10 ብር ነው::
ከተፈተነባት በለጋነት ወራት በጨቅላነት እድሜ
አውጣላት ላስር ብር ደም የሚል ስያሜ::
አረንጓዴ# ቢጫ# ቀይ
ልምላሜ# ተስፋ እና ደም
ከዚህ በላይ ትርጉም ከዚህ በላይ ፍቺ የትም ሀገር የለም::

ናሆም ታደሰ


(የሰው ልጆችን ባህሪና እጣ ከሚናገሩት የወራት ኮከቦች በግንቦት ወር በተወለደ ሰው ኮከብ ላይ የተመሰረተ ግጥም)
ኮከብሽ ሲፈታ
ግንቦት ነው ውልደትሽ በግለቱ ፀሀይ
ሀሩር ሲገባደድ ለዝናብ ሩብ ጉዳይ::
እና በዚህ ወር ላይ ወደምድር የመጣ
ውዝግብግብ ነው እድሉ አከራካሪ እጣ
ግትር ነው ልቦናው ጨካኝ በባህሪ
እማ እንዲ ነሽ እንዴ ለሰውም አትራሪ?
ደሞ ዝቅ ብሎ ኮከብሽ ሲነበብ
ግሩም አይምሮ አለው የሰላ አስተሳሰብ::
ይህን ማን ይክዳል?
እጅሽ ካላጠረ የሙት ልጅ ካበላ
ከወዴት ሊመጣ ካንቺ በላይ የሰላ?
በፈጠረሽ እማ
ይህን ስል አይምሮ የአብራክሽ ክፋይ ለምነው ያልወረሰው?
ወይ አንቺ ራስ ወዳድ ወይም ደሞ ልጅሽ ማሰብ ያቃታው ነው ::
ትዝ ይልሻል እማ በሳት ዳር ጨዋታ
የእግሮችሽን ቅጥነት የጠየኩሽ ለታ?
አንቺማ ዋሸሺኝ እንዳይቀንስ ፍቅሬ
የእሳት ልጅ እሳት ነው ደረስኩበት ዛሬ::
እጣ ክፍሉ ሆኖ ግንቦት የወለደው
ቤት መዋል ይጠላል እግረኛ ተጓዥ ነው::
መጓዝ አይጠላም መገስገስ ደግ ነው
ግን እማ ያንቺን ጉዞ ዳና ስ ያረገው
ወደላይ ነው እንዴ ልቴጅ የፈጠረሽ?
የመሬት ስበት ነው እዚያው የመለሰሽ?
አንቺ ብትሸሽጊኝ ሀቅኮ ንጋት ናት አትቀር ተደብቃ
ጉደኛ ኮከብሽ መች በዚህ ሊያበቃ…
በዚህ ወር ዓለምን የተቀላቀለ
ብዙ ልጅ የለውም የሚል ሀረግ አለ::
እዚ ላይ እውነት አለው ካላደለሽ ባርኮ
ካብራክ የወጣ ሁሉ ልጅ አይደለምኮ::
ስል ካማጠ ሆድሽ መጋዝ ከፀነሰ
ባቢሎን ካረገዝሽ ሳይቋጭ የፈረሰ
ማህፀንሽ ከከዳ ጭድ ከበቀለበት
መወለድ ቋንቋ ነው ፊደል ነው ልጅነት::
እማኮ ትንፋሽሽ
ቁርጥ ቁርጥ ይላል ብዬ ስጠይቅሽ
ደበቅሽኝ ደዌሽን አልችል አለ አንጀትሽ::
እውነቱ ግን እማ…
የዚህ ወር ዘለላ ገና ከጥንስሱ
ትንሽ ደከም ይላል አተነፋፈሱ::
ሳንባሽም ደከመ? እና ምን ቀርቶሻል?
ትንባሆ ገሎሻል ወይ ድመት ወልደሻል
ምንድነው የደበቅሽኝ? እስትንፋስ ቀልድ ነው?
አዳምኮ ያኔ ህይወቱን የዘራው በጌታ ትንፋሽ ነው::
ደሞ ዝቅ ስንል ኮከብሽ እንዲ ይላል
ግንቦት የሚወለድ ጆሮውንና አንገቱን ብዙ ግዜ ያመዋል::
እዚህ ላይ ፉርሽ ነው ቀባጣሪ ኮከብ!
ለሀዘን ፅዋ አርጎሽ ለመከፋት ሰበብ
አንድ ለናቱ ሆነሽ በጤነኞች መሀል
ምን የቀረሽ አለ ያልታመምሽው አካል?
ቆይ እንጂ ረጋ በይ ስሚ ኮከብሽን
ሩቅ ማሰብ ሩቅ ማለም ቶጃለሽ ያለሽን
በዚ እንኳ አትታሚም አንደራደርም
ያንቺን የሩብ ግማሽ ዘንዶም አያልምም::
ግን እማ ንገሪኝ
ሲመሽ አስተዳድሮሽ ሲነጋ ሚከንፈው
የተካነ ጠበብት ሎሬት የማይፅፈው
ብርሀን የሚፈራው ያ ጭሱ ራእይሽ
ለምፃት ነው እንዴ የሚፈታው ህልምሽ?
ጉዱን ለቀባሪው ማርዳት ባይሆንብኝ
ልንገርሽማ እማ ምን እንዳነበብኩኝ
ካስራ ሁለት ወር ነጥቆ ግንቦት የወለደው
ስነ-ፅሁፍ ወዳድ ጥበብ አድናቂ ነው::
ይሄማ ግልፅ ነው ጥበብሽ መች ታጣ
ድሮ አንቺ የሌለሽን 'ኔ ከየት ላመጣ?
ግን እማ እኔ ያልገባኝ…
መቶ ሀያሲ ታቅፎ ሺ ሎሬት ደርድሮ
ከእልፍኝ በማይወጣ በጭብጨባ ታስሮ
የግዜ እርከን መሆን የጠቢብ ጣራ ነው?
ምን ካንቺ ባላውቅም ጥበብ ማለትኮ ሀገር ሲቀይር ነው::
ግርምቴን ልቀጥል? እማ አታዝኚብኝም?
ብርቅኮ ሆኖብኝ ነው! ጉደኛ ኮከቤ ምን አለ አትይኝም?
የዚህ ወር አርበኛ ከሌላ ሚለየው
ባካልም ባይምሮም የተዋበ ሰው ነው::
ይገርማል አይደለ? ይህን እንኳ አታቂም
ውበት በባህሪው ለተመልካች እንጂ ለራስኮ አይታይም::
ለምን ይመስልሻል ያ ሁሉ ተጋዳይ
ጦር ጎራዴ ይዞ የመጣው ባንቺ ላይ?
ጀግና የተጣላብሽ ቆንጆ ነሽ እመኚኝ
ይልቅ እሱን ትተሽ ምን ገረመህ በይኝ
እንዴት የተዋበ አስቀያሚ ይወልዳል?
ከተሳለ አይምሮስ ጭፍጋግ አስተሳሰብ እንዴት ይፈጠራል?
ምን ዥንጉርጉር ቢሆን ሺ ቢያደላ የእናት ሆድ
ተባርኮ ፀንሶ ያለም መርገም ይውለድ?
አዎ አንቺማ ሳቂ…ደሀውን ይግረመኝ
ወዳጄ ኮከብሽ ጠንካራ ፍላጎት እንዳለሽ ነገረኝ::
አሁን እኔ ልሳቅ…
እማ አሁን ፍላጎት ምን ያደርግልሻል?
ምሰሶ ያላርማታ ብቻውን ሲፀና የት ሀገር አይተሻል?
ለፍላጎትማ አዳምስ ሲፈጠር
የጌታውን ወንበር ተመኝቶ አልነበር?
እስኪ ብቻ ተይው…
ይህ ሁሉ በባህሪሽ የባህር ውሀ ነው ቢቀዝፉት አይደርቅም
እንኳን በኔ አንደበት በራስሽ አያልቅም::
እንዲ እንዳስገረምኩሽ አልቀርም አትስጊ ብዙ አወጋሻለው
ደሞ ሌላ ጊዜ የልጅሽን ኮከብ የኔን ነግርሻለው::

 ናሆም ታደሰ



Wednesday, July 22, 2015

የኔ ቢጤ
አምስት አስር ሳንቲም ስለምን ያየኝ ሠው
ያገሬው ከበርቴ ዝና የተላበሰው
እራሱን አዋርዶ እራሱን አቅሎ
ሲጠራኝ ሰማሁት የኔ ቢጤ ብሎ::
ያንተ ቢጤ ብሆን ሀብታም ባለዝና
ምን ያዘረጋኛል እጄን ለልመና?

የለጋሹ ቢጤ

Friday, June 26, 2015



ለፊደል እና ለትውፊት የሬድዮ ፕሮግራም የተገዙት መቅረፀ ድምፆች የውሀ ሽታ ሆነዋል

ለፊደልና ለትውፊት የሚያገለግል ኋላ ቀር መቅረፀ ድምፅ
የፊደል እና የትውፊት የሬድዮ ፕሮግራም በድምሩ የሁለት ሰአት የአየር ሽፋን የያዘ ሲሆን በሶስት መቅረፀ ድምፆች ብቻ ሲሰራ ቆይቷል። 

መቀሌ ዩንቨርስቲ ለዚህ በጀት መድቦ ተጨማሪ መቅረፀ ድምፆች እንደተገዙ ከተነገረ ሰንበትበት ያለ ሲሆን እስካሁን ድረስ ግን የመቅረፀ ድምፆቹ ወሬ የውሀ ሽታ ሆኖ ሰንብቷል። 

የመቀሌ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ትምህርት ክፍል ዲን የሆነው መምህር መብርሀቴን ይህን ችግር በተደጋጋሚ ለበላይ አካላት አሳውቆ ምንም አይነት መፍትሄ እስካሁን እንዳልተገኘ እና ከዛሬ ከነገ መቅረፀ ድምፆቹ እጃችን ይገባሉ በሚል ያልትጭብጠ የስፋ እየተጓዙ እንደሆነ ተናግሯል። 
 በማከልም “እስከ አርብ ግንቦት 21 2007 ዓ.ም አምስት መቅረፀ ድምፆች ይደርሱናል” ሲል የተለመደ የተስፋ ቃሉን አስቀምጧል። የመቀሌ ዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንትም ዶክተር ክንደያ ገ/ህይወትም በበኩላቸው “ይህ በማንኛውም የስራ ዘርፍ ሊያጋጥም የሚችል ችግር ስለሆነ ተማሪው በትእግስት ሊሰራ ይገባል። መቅረፀ ድምፆች ተገስተዋል። በቅርቡ እጃችው ይገባሉ” ሲሉ ያላቸውን እስተያየት ገልፀዋል።